Pages

Wednesday, June 28, 2017

"ዘውጌኝነት" እና "ዘውግ-ዘለልነት"…?

የዘውግ ብሔርተኝነትም ይሁን ኢትዮጵያዊ ኅብረብሔርተኝነት አተያዮች በዘውግ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሁለቱም ዜጎችን የሚመለከቱት የዘውግ ምንዝር (ethnic subjects) አድርገው ነው። ስለዚህ ይለያያሉ ማለት አይቻልም።
ለብዙዎቹ ችግሮቻችን ፍቱን መድኃኒት አድርጌ የምወስደው፣ ጉዳዩን በዘመን ቁመት እና በዓለም ሕዝቦች ታሪክ አግድም መመልከት ነው። ዓለም በበቂ ሁኔታ የምንማርባቸው ስኬቶች እና ውድቀቶች አሏት። ዘውጌኝነት፣ ብሔርተኝነት እና ዜግነት የመሳሰሉትም የብቻችን ጉዳዮች አይደሉም። ዓለም በየፈርጁ የዳከረችበት እና እየዳከረችበት ያለ ችግር ነው። ስለዚህ ጥያቄውን በቅጡ ለማበጃጀትም ይሁን፣ አዋጭ መልስ ለመፈለግ ከሰው ልጆች እንደአንድ የሚያደርገንን ታሪክ የምናውቀውን ያክል ማሰስ ያስፈልጋል። ይህን ከጠቆምኩ በኋላ ወደ የበኩሌን ለመሞከር ወደ አጀንዳዬ እዘልቃለሁ።

የዘውግ ብሔርተኝነት ምንድን ነው?

የዘውግ ብሔርተኝነት (ethnonationalism) የአንድ ዘውግ (ethnic) ቡድን ነጻ አገር እንዲመሠርት ወይም ከመገንጠል ወዲህ ያለውን የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል የሚደረግ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ነው።

የዘውግ ማንነት በኢትዮጵያ ልማዳዊ አሠራር በወላጆች ማንነት ነው የሚወሰነው። እናትና አባታቸው ከተለያዩ ዘውጎች የተወለዱ ዜጎች በተለምዶ የአባታቸውን የዘውግ ሐረግ ነው የሚወርሱት። ዜጎች በአንድ ክልል ተወልደው፣ የአካባቢውን ቋንቋ፣ ባሕልና ወግ አውቀው ቢያድጉም ከአካባቢው ዘውግ የተለየ ዘውግ ካላቸው ወላጆች ከተወለዱ የአካባቢው ዘውግ አላቸው አይባልም። ማለትም፣ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከአማራ ልጆች ተወልደው ያደጉ ልጆች በዘውግ ብሔርተኞች እንደኦሮሞ አይቆጠሩም። በሕግ የመምረጥ እና መመረጥ መብት ቢኖራቸውም በልማድ ተቀባይነት የማግኘት ዕድላቸው ግን አነስተኛ ነው። ነገሩን ይብስ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ በሌሎች ማኅበረሰቦች መሐል የሚያድጉ ልጆች ከአደጉበት ማኅበረሰብ ይልቅ ዘውጋቸውን ከወላጆቻቸው በደም ለመውረስ የመፈለጋቸው ልምድ ነው፡፡

የዘውግ ብሔርተኝነት ንቅናቄዎች ከዘር (race) ንቅናቄዎች ጋር በትይዩ ሊታዩ ይችላሉ። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ያሉ ዘውጎች በፊት ቅርፅና የቆዳ ቀለም ሊገለጽ የሚችል ልዩነት ባይኖራቸውም (የዘር ልዩነት ባይኖርም)፣ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ግን ተቀራራቢነት አላቸው። ሁለቱም "በማንነታችን ምክንያት የመብት እና ዕድል አድልዎ ይደረግብናል" ይላሉ። የሚገጥሟቸውም ተግዳሮቶችም ተቀራራቢነት አላቸው፤ ለምሳሌ ያክል 'Black Lives Matter' (የጥቁር ነፍስም ዋጋ አለው) በሚለው የጥቁሮች ንቅናቄ ላይ 'All Lives Matter' (የሁሉም ሰው ነፍስ ዋጋ አለው) ነው መባል ያለበት እንደሚሉት ሁሉ፣ በኛም አገር ለምሳሌ 'Because I am Oromo' (ኦሮሞ ስለሆንኩ) እንዲህ ደረሰብኝ በሚለው ፈንታ 'Because I am Ethiopian' (ኢትዮጵያዊ በመሆኔ) ነው መባል ያለበት የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።

Wednesday, June 14, 2017

የቂሊንጦ እሳት፣ ወላፈኑን የቀመሱት እና በሰበቡ የተከሰሱት

(ፎቶ፤ ደህናሁን ቤዛ)

ይህ ታሪክ በደርግ ዘመን የተፈፀመ አይደለም። በኢሕአዴግ ዘመን የተፈፀመ የበደል ታሪክ ነው።… የምነግራችሁ ታሪክ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ "ለተሀድሶ ሥልጠና" ወደ አዋሽ ሰባት የፖሊስ ካምፕ የተጓዝኩትን ያስታውሰኛል። "ከሥልጠናው" ሰነዶች በአንዱ ላይ፣ በደርግ ግዜ ይፈፀሙ የነበሩትን የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች "ሰምቶ ማመን የማይችል ትውልድ ተፈጥሯል" ይላል። አባባሉ የኢሕአዴግን በትር እየቀመሱ ለኖሩ በጣም ያስቆጣል። ቀጥሎ የማወራላችሁ ታሪክ የደናሁን ቤዛ ታሪክ ነው። ደናሁን ደርግን የማያውቅ ወጣት ነው። ኢሕአዴግን ብቻ እያየ አድጎ ኢፍትሐዊነቱን መቀበል ያቃተው የመርሃዊ፣ ጎጃም ልጅ ነው።

ደናሁን በእነዘመኑ ካሴ በእውቄ መዝገብ፣ በፀረ ሽብርተኝነቱ አዋጅ ከተከሰሱት 9 ሰዎች 3ኛው ነው። ባለፈው ሳምንት የእስር ግዜውን ጨርሶ በፍቺ ተሰናብቷል። ከአባሪዎቹ መካከል አሸናፊ አካሉ በቂሊንጦ እሳት አነሳሽነት ክስ ተመሥርቶበታል። አንሙት የኔዋስ የተባለው ደግሞ ይህንን ለዐቃቤ ሕግ ከሚመሰክሩት መካከል ሥሙ ተጠቅሷል።
ቁጥቡን ደናሁንን የተፈታ'ለት አግኝቼው ነበር። ብዙ ነገር ተጨዋወትን። ሸዋሮቢት ወስደው በካቴና አስረው ሰቅለው ሲገርፉት ካቴናው የእጁ ወርች ላይ፣ እግሩ የታሰረበት ገመድ ደግሞ ከቁርጭምጭሚቱ በላይ ያወጡትን ሰምበር እያሳየኝ ነበር። ይህ ድርጊት ከተፈፀመበት 9 ወር ገደማ ቢሆንም ጠባሳው እስካሁን ከሰውነቱ አልከሰመም። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ምንም ያልሠራውን ወንጀል ባለማመኑ ይመስላል፣ ወይም ደግሞ ምናልባት ሌሎች እስረኞች ሥሙን ስላልጠቀሱ ከጓደኞቹ ቀላቅለው አልከሰሱትም፤ አባብለው ምስክር እንዲሆንባቸውም ማድረግ አልቻሉም።

የደናሁን ጀብዱ
የደናሁን ጥንካሬ የመጣው፣ ምናልባትም ካለፈው ልምዱ ይሆናል። ደናሁን እንዳጫወተኝ በትውልድ አካባቢው ያለውን ኢፍትሐዊነት ከጓደኞቹ ጋር መቃወም የጀመረ ሰሞን ከመኢአድ ሰዎች ጋር እየተገናኘ ማውራት ጀምሮ ነበር። አንድ ቀን ግን ድንገት በደኅንነት ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ዋለ። ወዲያው አንድ ትዕዛዝ ተሰጠው። "በል ጓደኞችህን ደውልና ቅጠራቸው።" ደናሁን ደወለ፤ "ሃሎ እከሌ፣ እኔ ተይዣለሁ እራሳችሁን አድኑ።" ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ሲደበደብ አደረ። እስከ ማግስቱ ጓደኞቹ ስልኩ ላይ መደወል ተያይዘዋል። ደኅንነቶቹ ሁለተኛ ትዕዛዝ ሰጡት፣ "በል አንሳውና አምልጫለሁ፣ የት ላግኛችሁ?" በላቸው አሉት። 'እንግዲህ ከዚህ በላይ አልችልም፤ ከገባቸው ይግባቸው' ብሎ እንደታዘዘው አደረገ። "እዛ የምናውቀው ቤት ና" አሉት። ሒድ ምራ ተባለ። ደናሁን ከኋል ከኋላው ታጅቦ እየመራ እያለ፣ ጓደኞቹን አሳልፎ መስጠት አላስቻለውም። ድንገት ፈትለክ ብሎ ሮጠ። ጓደኞቹንም ጠርቶ አብረው አመለጡ። በግዜው የታያቸው አማራጭ መሸፈት ብቻ ነበር። እዚያው የተገኘው ጫካ ውስጥ፣ የተገኘውን መሣሪያ ይዘው ሸፈቱ። የደናሁን እናት ለመያዣነት አንድ ቀን ታሰሩ። ደናሁን አሁንም ሳይማረክ ሲቀር ተፈቱ፤ ደናሁን ሌሊት ሔዶ ዓይናቸውን አየ። ከዚያ በኋላ በሌላ ቀን በተቀነባበረ ዘመቻ ከነጓደኞቹ በቁጥጥር ሥር ዋለ።