Pages

Thursday, November 8, 2012

የአዲስ አበባ ከተማ እና ምርጫዋ

From Addis Ababa, Ethiopia

አዲስ አበባ 125ኛ ዓመቷን እያከበረች ነው፡፡ በከተማይቱ ልደት ሰሞን እናትና አባቷ (በመናገሻ ከተማነት የቆረቆሯት አጤ ምኒልክ እና ስሟን ያወጡለት እቴጌ ጣይቱ) ስማቸው ሲነሳ አልሰማሁም፡፡ ይልቁንም ላለፉት 21 ዓመታት በፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ መሪነታቸው በእጅ አዙር የዘወሯት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ እና በየመንገዱ ዳር በቆሙ ‹ቢልቦርዶች› ላይ ከከተማይቱ የመሠረተ ልማት አውታሮች ፎቶ ፊት ለፊት በጉልህ በተቀመጡ ምስሎቻቸው ታጅቦ ታይቷል፡፡

የክብረ በዓሉን ክንውን እንዲያዘጋጅ የኢሕአዴግ ሰዎች የሚመሯቸው ዋልታ እና ፋና ጥምር-ድቅል የሆነው ዋፋ የማስታወቂያ ድርጅት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ ምናልባትም የዚሁ የፓርቲ ጥገኝነት ጉዳይ ይሆናል መለስን በግምባር ቀደምነት የከተማይቱን ቆርቋሪ አስዘንግቶ ያስጠቀሳቸው፡፡

ለነገሩ ይህን ጽሑፍ ለማሰናዳት ያነሳሳኝ የክብረ በዓሉን ዐብይ-ሰብ (figure) ለመሰየም አይደለም፡፡ ስለከተማይቱ እያነሳሁ ይህንን ያፈጠጠ ስህተት ሳልነቅስ ማለፍ ስላልሆነልኝ ነው፡፡ የጽሑፌ ርዕሰ ጉዳይ ሚያዝያ ወር ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ከሀገር አቀፍ ምርጫ በሁለት ዓመት እንዲዘገይ የሆነው፣ በምርጫ 97 ከአንድ ወንበር በስተቀር ሁሉንም የከተማዋን ምክር ቤት መቀመጫዎች አሸንፎ የነበረው ቅንጅት ምክር ቤቱ ለመግባት ባለመፍቀዱ  ማሟያ ምርጫ እስኪካሄድ በተፈጠረው መዘግየት ሳቢያ ነው፡፡

ሀገሪቱ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በላይ ባላየችባቸው ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ አዲስ አበባ አምስት ከንቲባዎችን ለማየት ታድላለች፡፡ አንዴ ግዜያዊ የባለአደራ ከንቲባ ስታስተናግድ ቀደም ብሎ ደግሞ ‹‹ተበለሻሸች›› ተብሎ - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በሚፈቅደው መሠረት - ምክር ቤቷ ፈርሶ በድጋሚ እንዲገነባ ተደርጎ ነበር፡፡ በነዚህ ጊዜያት ከተሠሩ ሕንፃዎች እና መንገዶች በተጨማሪ በተለይ ሕዝቡን ያማከለ ሥራ የሠሩት አርከበ ናቸው፡፡ አርከበ የኮንዶሚኒዬም ቤቶችን እና አርከበ ሱቆች ተብሎ በማኅበረሰቡ የተሰየሙላቸውን ጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ ቤቶች ያስጀመሩ ከንቲባ ናቸው፡፡

በዐሥር ክፍለከተሞችና ከ100 በላይ በሆኑ ቀበሌዎች (አሁን ወረዳዎች) የተከፋፈለችው አዲስ አበባ ከ5 እስከ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎች እየዋሉ እንደሚያድሩባት ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው ከ3 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ለምርጫ ብቁ የሆኑት ደግሞ 2.2 ሚሊዮን የሚጠጉት ብቻ ናቸው፡፡

Monday, October 15, 2012

የኛ ኃይል



ዞን ዘጠኝ የተወሰደ


“ፒያሳ፤ መሐሙድጋ ጠብቂኝ” በመሐመድ ሰልማን የተጻፈ እና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ኢ-ልቦለዳዊ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት  አማካይነትመጽሐፉን የመገምገሚያ ዝግጅት አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም ቀርቦ ነበር፡፡ በውይይቱ መሐል የመጽሐፉ ዝነኝነት ምንጮች ምን ምን ናቸው የሚል ውይይት የነበረ ሲሆን ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ‹‹ደራሲው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ጸሐፊ የነበረ›› መሆኑን እና ‹‹ጽሑፎቹም በአዲስ ነገር ጋዜጣ እና ድረገጽ ላይ ወጥተው የነበሩ›› መሆናቸውን ጠቀሰ፡፡ ውይይቱ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መታሰቢያ ይመስል፣ የትዝታ ጫወታው ተጧጧፈ እናም ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ የሚከተለውን ሲናገር ረዥም ጭብጨባ አዳራሹን አደመቀው ወጣቱ አስተያየት ሰጪ በንግግሩ መሃል የተጠቀመው እና ጢም ብሎ የሞላውን አዳራሽ በጭብጨባ ያናጋው ንግግር የሚከተለው ነበር፡፡

‹‹ይህ ትውልድ በአዲስ ነገር ጋዜጣ የሚደራደር ትውልድ አይደለም፡፡››

ጉዳዩን አስገራሚ የሚደርገው ወጣቱ ይህንን የተናገረው አዲስ ነገር ጋዜጣ መታተም ካቆመች ከሁለት ዓመታት በኋላ መሆኑ ሲሆን፣ አጋጣሚው የጋዜጣዋ መንፈስ በበርካቶች ልብ ውስጥ በትኩስነት መኖሩን የሚናገር ነበር፡፡

ዛሬ፣ ጥቅምት 5/2005 የዓለም የጡመራ የተግባር ቀን (Blog Action Day 2012) “የኛ ኃይል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ የጡመራ የተግባር ቀን በየዓመቱ የሚከበር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦማሪዎች በሙሉ በአንድ ሐሳብ ዙሪያ የሚጽፉበት ቀን ነው፡፡ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2007 ሲሆን በተመሳሳይ  ዓመት ‹‹አካባቢ››፣ በ2008 ‹‹ድህነት››፣ በ2009 ‹‹አየር ለውጥ››፣ በ2010 ‹‹ውሃ››፣ በ2011 ‹‹ምግብ›› በሚል ሲካሄድ ዘንድሮ ደግሞ በ2012 ‹‹የእኛ ኃይል›› በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የዘንድሮው መሪ ቃል፣ ማኅበረሰብ፣ እኩልነት፣ ፀረ-ሙስና እና ነጻነትን በተመለከተ የኛ ኃይል ምን እንደሆነ በመስበክ እንዲከበር ታስቦ የተመረጠ ነው፡፡ አከባበሩ ቀላል ነው፤ አስተባባሪዎቹ እንዳስቀመጡት ‹‹profile someone or a group who inspires you by the way they made a positive influence… (ባመጡት አዎንታዊ ተጽዕኖ ያነቃቃችሁን የሆነ ሰው ወይም ቡድን በመምረጥ ጻፉ…)›› የሚል ነው፡፡

እኛም ጮክ ብለን ስናስብበት እና በጭንቅላታችን ያቃጨለችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ብቻ ሆነች፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ ለሁለት ዓመታት (ከጥቅምት 2000 እስከ ታሕሳስ 2002) ብቻ በስርጭት የቆየች ነገር ግን መራኄ አዘጋጇ መስፍን ነጋሽ የጋዜጣዋን ሁለተኛ ዓመት አስመልክቶ እንደገለፀው ‹‹አጭር ግን ረዥም ዓመት›› የኖረች ያክል የማትረሳ ጋዜጣ ናት፡፡

Tuesday, October 9, 2012

የኃይለማርያም ፲ ተግዳሮቶች

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ


የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኅልፈት ከተሰማ 50 ቀናት ሆኑት፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ቃለ መሓላ ከፈፀሙ ደግሞ 18 ቀናት፡፡ እነዚህ ከሁለት ሳምንታት እምብዛም ያልበለጡ ቀናት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን አያያዝ ለመገምገም በቂ አይደሉም ነገር ግን ‹‹ያባት ዕዳ ለልጅ›› በሚለው ብሒል መሠረት የመለስን ፈለግ በመከተል እና ባለመከተል መካከል፣ ሊያመጧቸው በሚችሏቸው ለውጦች እና ሕዝብ/አገር ከሚጠብቅባቸው ነገሮች አንፃር የሚጠብቃቸውን ተግዳሮት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለይ ከቪኦኤ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ጋር ባደረጉት የ40 ደቂቃ ቃለምልልስ፥ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተለየ አቋም እንደሌላቸው መታዘብ ይቻላል፡፡ ፓርቲውም ቢሆን የአቶ መለስን ውርስ ለማስቀጠል እንደሚተጋ በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ በተቃራኒው መለስ የሚባልላቸውን ያህል ውጤታማ እና ፍፁም አልነበሩም፡፡ ለዚህም ምስክሩ ሳይዘጉ የተዉአቸው የሚከተሉት አጀንዳዎች ናቸው፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ተግዳሮቶች ሁነው ይቀጥላሉ፡፡

Saturday, September 8, 2012

የ2004 ሒሳብ ሲዘጋ

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ


እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በዚህ ዓመትም ሰዎች ከፌስቡክ ውጪ እንዴት እንደሚኖሩ ለማወቅ ጉግል ውስጥ ፈልጌም፣ አስፈልጌም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ በፌስቡክ ውስጥ መኖሬን ቀጥያለሁ፡፡ በርግጥ ፌስቡክ ምንም አልጎደለበትም፤ እንኳን የሆነው የታሰበው ሳይቀር ይወራበታል፡፡ ለአብነትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርን ሞት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ፌስቡክ ምድር ላይ ካለው ‹እቤት-እመስሪያቤት› ምልልስ የተሻለ ፋይዳ ያለው ሥራ ለመስራት የተመቸ ዕድልም ይፈጥራል፡፡ የዳቦ ጉዳይ (bread winning) ሁላችንንም በየሙያችን ቢያሰማራንም፣ የምንናፍቀው እና የሚናፍቀን ሌላ ነገር የለም ማለት መቼም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የምንዋደደውን ያክል የምንወደውና የሚወደንን ዓይነት መንግስት ያገኘንበት ጊዜ እምብዛም ነው፡፡ ይህንን መናፈቅ እና መማከር ደንብ ሆኖ፣ በሌላም፣ ዓመቱን ሙሉ በጻፍናቸው ነገሮች ያስደሰትነው ሰው እንዳለ ሁሉ ያስቀየምነው የለም ማለት ዘበት ነውና፣ ያው የግል ጥቅም ይዞን አለመሆኑ ታውቆ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ይቅር መባባልን የመሰለ ነገር የለም፡፡

በዚህ ዓመት በፌስቡክ ገጼ ላይ ያሰፈርኳቸውን እና ከወዳጆቼ ጋር ቅኔ የተዛረፍኩባቸውን ግጥሞች በአንድ መድብል ‹‹የፌስቡክ ትሩፋት›› በሚል ጠርዠዋለሁ፡፡ ማንም ቢፈልግ እዚያው ባለበት ማንበብ፣ ወይም ዳውንሎድ ማድረግ ይችላል፡፡ አምና ሁለት ሺህ ሦሰትን በአርባ ሁለት በሚል በ2003 የጻፍኳቸውን ጦማሮች አንድላይ ቢጠረዙ መልካም ነው በሚል ማስቀመጤ ይታወሳል፡፡ አሁንም ዘንድሮ የሞነጫጨርኳቸውን እዚህ አስቀምጫለሁ፡፡

በስህተቴ ያረማችሁኝን እና የነቀፋችሁኝን፣ በብርታቴ ላይ አበርታች የሆነ አስተያየታችሁን ለሰጣችሁኝ፣ በዝምታ ስታነቡኝ ከርማችሁ መንገድ ላይ ስታገኙኝ ለነገራችሁኝ እና ለሌሎቻችሁም ሁሉ ምስጋናዬ እንዲደርሳችሁ ከጉልበቴ ሸብረክ ማለቴን እንደምታስቡልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አዲሱ ዓመት ሕልማችን የሚሞላበት፣ ለፍቅራችን ዋጋ የምንሰጥበት ይሁን፤ አሜን!

በ2004 የተጻፉ
  1. መንግስት ያልቻለውን እኛ ብንሞክረውስ?
  2. ሞክሮ መሳሳት እና ከስህተት መማር
  3. ፍቅር፤ ከፍቅር እስከ መቃብር (ልቦለድ)
  4. የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ለተቃዋሚዎች
  5. የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና አንዳንድ አካላት
  6. ኢትዮጵያውያን ለምን ዲቪ አይሞሉ?
  7. ደረሰኝ ሳይቀበሉ፥ ሒሳብ አይክፈሉ
  8. አሰብ የማን ናት?” በጨረፍታ
  9. ይህ - የታገልንለትን ጉዳይ አለማወቅ ነው
  10. አዎንታዊ ሀቆች ስለሊቢያ እና ጋዳፊ (Positive facts about Libya and Gadaffi) (ፌስቡክ ላይ ብቻ)
  11. ኢትዮጵያ ከኢሕአዴግ በኋላ፤ ሰጥቶ የመንጠቅ ዘመነ መንግስት
  12. In T1me - ጊዜ ገንዘብ (ገንዘብ ጊዜ) ቢሆን ኖሮ!
  13. “Every nation deserves its government” - ኦቶ ቮን ቢስማርክ
  14. የኢሕአዴግ ‹‹ትርፍ›› እና ኪሳራ
  15. ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ እያለች ሃገር የላቸውም
  16. የዳዊት ከበደ እና የተመስገን ደሳለኝ ወጎች
  17. ጨርቆስና ቦሌ - ሕይወትን እኛ እንደኖርነው!
  18. እስኪ ስለዋጋ - ቆም ብለን እናውጋ!
  19. ገመና 2 ሰው ለሰው፣ ጀግንነትና ኢትዮጵያ
  20. ሰማንያ ሚሊዮን እስከምንደርስ እንታገላለን
  21. የፈረንጅ አምልኮ በኢትዮጵያ
  22. የኢትዮ ቴሌኮም ቁልቁለት
  23. አፍንጫ ሲመታ ዓይን አያለቅስም ወይ?
  24. የሐበሻ አምልኮ በኢትዮጵያ
  25. አማርኛ በመዝገብ ላይ
  26. የቫለንታይን ጉርሻ ለወንዶች፤ የአዲስ አበባ ሴቶችን እንደታዘብኳቸው - ልማላችሁ! (ፌስቡክ ላይ ብቻ)
  27. ኑሮ በአገርኛ÷ ጾም ይበዛበታል!
  28. የአሜሪካ ኮንግረስ እና ሌሎችም ከኢትዮጵያ ፓርላማ መማር የሚገባቸው!
  29. ሦስት ሰዓታትን በግዞት (ፌስቡክ ላይ ብቻ)
  30. እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን
  31. እንደ እርሳቸው ያለ ፊትም አልነበረ፤ አሁንም የለ፤ ምናልባት፣ ምናልባት ወደፊት ሊኖር ይችላል!
  32. ሕዝቦች ግለሰብን ይጨቁናሉ!
  33. እውትምሰሚ ያጡ ድምፆች!’
  34. መራመድና ባሉበት መሽከርከር፤ ሁለት የኑሮ ፈሊጦች
  35. እስኪ እንጠያየቅ፤ አገራችን የት ነው? (መጠባበቂያ ካስፈለገ)
  36. የቴዲ አፍሮን አልበም ያልገዛሁባቸው 5 ምክንያቶች
  37. ደጉ ኢትዮጵያዊ፤ ከልብ ካለቀሱ እምባ እንደማይገድ ያስመሰከረ ስብስብ
  38. የኢትዮጵያ መንግስት መጠላቱን የሚያሳብቁ ምልክቶች
  39. ከአከሌን አሰሩት እስከ አከሌን አገዱት!
  40. አብዮት ወረት ነው!
  41. የጋንዲ፣ ኪንግ እና ማንዴላ መንፈስ
  42. ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይስ የለም? (እርስዎ ምን ይላሉ?)
  43. የመፈረጅ ፍራቻ እና የመፈረጅ አደጋ
  44. 21 ዓመት በኋላ (ዴሞክራሲ ሲሰላ)
  45. አሸባሪፊልምም ይታገድ ጀመር (በነገራችን ላይ ከወራት በኋላ ድጋሚ ለአንድ ሳምንት እንዲታይ ተደርጓል)
  46. የአንድ ኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ታሪክ
  47. እነአልበርት አይንስታይን ስለዘንድሮው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ይላሉ?
  48. Hookah እና አሜሪካ
  49. የተመቻቸ ጊዜ መጠበቅ?
  50. አምስት የኢትዮጵያ ጠላቶች
  51. የባለፀጋዋን አገር ዜጋ፤ አቶ ድህነትን እናስተዋውቅዎ
  52. እውነቱ እና ፍርሃቱ
  53. የእንቆቅልሹ እንቆቅልሾች
  54. ጫወታ ስለየኦሎምፒክ ጫወታዎች
  55. ፋጡማ ኖረች አልኖረች፣ ጳጳሱ ኖሩ አልኖሩ…?
  56. የመለስ ሁለት መልክ
  57. ነውርን ማን ፈጠረው?
  58. በቁማቸው ከገደሉት በሞታቸው የገደሉት
  59. ኢሕአዴግ ቀይ እስክሪብቶ እኔ እንደወደድኩት (ዞን ዘጠኝ ላይ)
  60. ፎንቱ ፎኒፍ ሪፈታ ጄናን ኢቲሌን ጂቢቻ ካቴ(ዞን ዘጠኝ ላይ)
  61. የመለስ ዜናዊሀሁበስልጣን ጎዳና (ዞን ዘጠኝ ላይ)
  62. እውነት እና እስር ቤት (እስካሁን ለሰው ያላሳየሁት/ልቦለድ)

Saturday, September 1, 2012

በቁማቸው ከገደሉት በሞታቸው የገደሉት

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ


የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሞት በብዙዎች ጉንጭ ለሁለት ወር ሲጉላላ ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግስት ከተረጋገጠ ይኸው ሁለት ሳምንት ሊሆነው ጥቂት ቀናት ቀሩት፡፡ መንግስት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት እስከዕለተ ቀብራቸው በማወጁ ባንዲራም ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ነው፣ መገናኛ ብዙሐንም ሙሉ ትኩረታቸውን በዚያው በሐዘኑ ጉዳይ ላይ እንዳደረጉ ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ የጡረተኛ ሚኒስትሮችን ጥቅማጥቅም የሚዘረዝረው የ2001 አዋጅ ላይ [አንቀጽ 11/1/ለ] ብሔራዊ የሐዘን ቀን አንድ ቀን እንደሆነ ይደነገጋል፡፡)

ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢሆን ሐዘን የማክረር ባሕላችን የተጋነነ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሠልስት ሳይቀር እየተሰረዘ የሦስቱ ቀን ሐዘን ወደሁለት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በነገራችን ላይ የሐዘን ቀናት ወደሦስት ቀናት ዝቅ እንዲሉ የተደረገው በአፄ ምኒልክ አዋጅ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ነበር፡፡ እንግዲህ በሰሞኑ፣ ሁለት ሳምንታት የዘለቀ የሐዘን ግዜ መቶ ዓመት ያህል ወደኋላ ተመልሰናል ማለት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር የሞተበት አገር ሕዝብ ማዘኑ አስገራሚ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በውዴታም ይሁን በግዴታ ይህንን ያህል ቀናት ማዘኑ ወይም እንዲያዝን ማድረጉ ብዙ ጥያቄዎችን ያጭራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምናውራውም ከዚህ ፈር ከለቀቀ የሐዘን ግዜ በስተጀርባ ስላሉ ጉዳዮች ነው፡፡

አንድ፤ ችግር ይኖር ይሆን?

አገሪቱ አሁን እየተመራች ያለችው በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ነው ቢባልም፣ ያንን የሚያስመሰክር ነገር አላየንም፡፡ የመንግስት ልሳን የሆኑት እነ አዲስ ዘመን ሳይቀሩ ‹‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር›› እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ከዚያም በላይ አሳሳቢው ግን በቶሎ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ማዕረግ በፓርላማ ምርጫ እንዲቀበሉ አለመደረጉ አጠያያቂ ነው፡፡ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በታወቀ በሦስተኛው ቀን ተመርጠው፣ ቃለመሓላ እንደሚፈጽሙ ቃል ተገብቶልን የነበረ ቢሆንም፣ መጀመሪያ ‹‹በአቡነ ጳውሎስ ቀብር›› በኋላም ደግሞ ‹‹የፓርላማ አባላት ሐዘናቸውን ይወጡ›› በሚሉ የማያሳምኑ ምክንያቶች ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ይሄ ቁርጥ ያለ ቀን ለማስቀመጥ ያለመወሰን ጉዳይ አሁንም በአቶ ኃይለማርያም ተተኪነት ላይ በግንባሩ ውስጥ (ከምስጢር ወዳድነቱ አንፃር) ስምምነቶች አለመኖራቸውን የሚያጠራጥር ነው፡፡

Monday, August 27, 2012

ነውርን ማን ፈጠረው?

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ሰሞኑን በሞት ስልጣናቸውን ስለለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር  ያለኝን ትዝታ ‹የመለስ ሁለት መልክ› በሚል ጽፌው ነበር፡፡ ጽሑፉ ውስጥ የመለስ አስተዳደር በተለይ የተመቻቸው የብሔር አባላት እንዳሉ በስም በመጥቀሴ ‹‹ዘረኛ ነህ›› የሚል ብዙ አስተያየት ተሰንዝሮብኛል፡፡ እነሆ ይህ አስተያየትም ይህን ጽሑፍ ወልዷል፡፡ ነውርን ማን ፈጠረው? በመጀመሪያም፡-

ነፃነት እና ልቅነት

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለድርድር የማይቀመጡለት አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴ በሕግ ተደንግጓል ወይም ተፈጥሮ ያጎናፀፈኝ ነው በማለት እንዳሻው አይናገርም፡፡ በተለይም ሐሳቡ የሚቀርብበት ሚዲየም ሰፊ ሲሆንና ብዙ ተደራሲዎች ሲኖሩት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት፣ መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት እና አሁን ስለሆነው ሳይሆን ነገ እንዲሆን ስለምንፈልገው በመሳሳት (ሳ ላልቶ ይነበብ) ነው፡፡ ሁሉንም በሒደት ወደታች አብራራቸዋለሁ፡፡

‹የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት› ያልኩት ሐሳባችንን የምንገልጽበት አገባብ (context) ተደራሲያኑ ጋር ሲደርስ ሌላ አንድምታ እንዳይኖረው የሚለውን ነው፡፡ ምናልባትም ያለፈው ጽሑፍ ውስጥ ‹ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከተሰሩ ሕንፃዎች መካከል አብዛኛዎቹ የትግራይ ልጆች ንብረት ናቸው› ማለቴ በአንባቢው ዘንድ የትግራይ ልጆች ሁሉ በኢሕአዴግ ስርዓት ተጠቅሟል የሚል ትርጉም ከሰጠ አቅጣጫ አስቷል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኔ በፃፍኩበት መንፈስ የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር ካላቸው ድርሻ (proportion) ጋር ሲወዳደር በስልጣን እና በከተማ ሃብት ይዞታ ላይ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው የሚል ነው፡፡

ይሄንን እውነታ እንዳላነሳ የሚያስገድደኝ አካል ሊኖር አይችልም፤ የአገላለፁ አቀራረብ ላይ ውይይት ሊደረግ ግን እንደሚችል አልደራደርም፡፡ ይልቁንም ይህንን ጉዳይ የማይወራ ‹‹ነውር›› ነው የሚሉት (የሚያነውሩት) የስርዓቱ ፈጣሪዎች ወይም ተጠቃሚዎች ራሳቸው እንደሆኑም ይሰማኛል፡፡

Friday, August 24, 2012

የመለስ ሁለት መልክ

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞት ‹‹ድንገተኝነት›› ብዙ ድራማዎችን አስከትሏል፡፡ መጀመሪያ ላይ ብዙዎች ተደሰቱ፣ ማታ ላይ ኢቴቪ ያነጋገራቸው ‹‹አንዳንድ ሰዎች›› የሰውየውን ታላቅ መሪነት ሲዘክሩ ያድናቂዎቻቸው ቁጥር ጨመረ፣ በጣም ማታ ላይ ወ/ሮ አዜብ ‹‹ተቀጣሁ፤ ምን አጥፍቼ ነው?›› በማለት ሙሾ ሲያወርዱ ‹‹የመለስ ታላቅነት›› የተገለፀላቸው ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አደገ፡፡ ልብ በሉ በሞታቸው የመጀመሪያ ዕለት ብቻ ሁለት የተለያየ ገጽታ ለመያዝ የበቁት መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው፡፡ ነገርዬው ግን አብሯቸው የኖረ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ-አምባገነን

መለስ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚመስል ነገር መስርተዋል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለው ቃል በሚዲያ ተደጋግሞ እንዲነገርም ይፈልጋሉ፤ ያለ እንዲመስል፡፡ በምርጫ ማሸነፍ ያለበት የእርሳቸው ፓርቲ ብቻ እንደሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ ደጋፊ እንዲሆኑ፣ ጋዜጦችና ጋዜጠኞ ስኬታቸውን ብቻ እንዲያወሩ ይፈልጋሉ፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሲሄድም የሚወስዱትን እርምጃ በ21 ዓመታት አመራራቸው አሳይተውናል፡፡

መለስ ሳያነቡት እንደማያመልጣቸው የነገሩን The Economist ከሞታቸው በኋላ በጻፈው ጽሑፍ ‹‹መለስ አምባገነንነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ሰርተዋል›› በማለት አስታውሷቸዋል፡፡


ኢትዮ-ኤርትራዊነት

መለስ ኦነግ፣ ኦብነግንና ምንም ሪፖርት የተደረገ ጥፋት ሰርቶ የማያውቀውን ግንቦት ሰባትን በአሸባሪነት ሲፈርጁ ለስንት እልቂት ሰበብ የሆነውን ‹‹ሻዕቢያ››ን አሸባሪ ያላሉት በእርሳቸው መስፈርት ስላልሆነ ከመሰላችሁ አትሸወዱ፡፡ ቤተሰባቸው ስለሆነ ነው፡፡ መለስ ለኤርትራ እና ለኢሳይያስ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ የ‹‹ትሮይ ፈረስ›› የሚለውን መጽሐፍ ካነበባችሁ ‹‹ኅወሓት››ን ማን ጠፍጥፎ እንደሰራው ይገባችኋል፡፡ በእናታቸው ኤርትራዊ የሆኑት መለስ ኅወሓት ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ለኢሳይያስ ኤርትራን የመገንጠል እና የአሰብ ወደብን የመቀማት ሕልም ተባባሪ ሆነዋል፡፡ በትግል ወቅት የሚሰነዘሩ ሐሳቦችን ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ባፍጢሙ አይደፋም›› የሚል መጽሐፍ በመጻፍ በጠብመንጃም በጽሑፍም ታግለዋል፡፡
አገር ወዳድ - የአገር ጠላት

መለስ - በተለይ በስልጣናቸው መጨረሻ ሰሞን አገር ወዳድ ለመምሰል ይጥሩ ነበር፡፡ በተቃራኒው ታሪካችንን በመቶ ዓመት ሲቀጩት፣ ባንዲራችንን ከተራ ጨርቅ በላይ ፋይዳ እንደሌለው ሲነግሩን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹አገር ማለት ሕዝቡ ነው›› ባሉበት አፋቸው ‹ለልማቱ (ለሕንፃና መንገዱ) ሲባል ሕዝቡ ይጎሳቆል› ብለውበታል፡፡ ልዩነቱ የሚጎሳቆለው ሕዝብ እና የሚጣሰው ሰብአዊነት የእርሳቸውን እና የቤተሰባቸውን በር አያንኳኳም፡፡ ኤርትራን ያህል ሃገር እና አሰብን የሚያህል ወደብ አሳልፈው ሰጥተው፣ መልሰው ደግሞ ባድሜን ለምታክል ቁራጭ መሬት 120 ሺ ሰው ይገብሩብናል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ድህነት

የመለስ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ‹‹በሁለት ዲጂት›› አድጋለች፡፡ ሕዝቡ ግን ከመቼውም የበለጠ ድህነት ውስጥ ገብቷል፡፡ የገንዘብ ግዥበቱ ዕድገት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም፡፡ እርግጥ ነው በርካታ መንገዶች ተሰርተዋል፣ ብዙ ሕንፃዎች ቆመዋል ነገር ግን ኢሕአዴግ በገባ በ10 ዓመቱ በቀን ሦስቴ አበላዋለሁ ብለው ቃል ገብተውለት የነበረውን ሕዝብ በ20 ዓመታቸውም አላበሉትም፡፡

እውነቱን እየተነጋገርን ስለሆነ የተሰሩት ሕንፃዎች የማን ናቸው የሚለውን ጥያቄም መልሰን እንለፍ፡፡ በፊት በታታሪ ሰራተኝነታቸው የኢዲስ አበባን ግማሽ ሃብት ተቆጣጥረው የነበሩት ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ጉራጌዎች ነበሩ፡፡ ዛሬስ? ኢሕአዴግ ከገባ ወዲህ የተሰሩትን ሕንፃዎች ብትቆጥሩ ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ባለቤት የትግራይ ልጆች ናቸው፡፡ በ20 ዓመት ይህን ሁሉ ሀብት ያፈሩት በምን ጥበብ ነው?

ንግግር አዋቂው ተሳዳቢ

ንግግር አዋቂ (አንደበተ ርቱዕ) ሰዎች አይሳደቡም፤ ምክንያቱም በንግግራቸው ማሳመን ይችላሉ፡፡ ስድብ በንግግር ማሳመን ያልቻለ ሰው ውጤት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ንግግር ሆነ እንዲሁም በጥቅሉ አዋቂነታቸው በሰፊው ይወራላቸዋል፡፡ ይህንን ግን በቅጡ ላጤነው የቱ’ጋ እንደሆነ ለማወቅ ይቸግራል፡፡ አንደበተ ርቱዕነት በንግግር ለዛ ማሳመን እንጂ ቃላትን በመሰንጠቅ፣ አዳዲስ የስያሜ ባጅ በመለጠፍና በማደናገር የሚፈጠር አይደለም፡፡ ስለፖሊሲያቸው ሲጠየቁ ‹ፊዚካል ፖሊሲ› የሚባል የለም ‹ፊስካል ፖሊሲ› ነው የሚባለው የሚል ዋና መስመሩን የሳተ ‹‹የፉጨት›› ሌክቸር መስጠት ያምራቸዋል፡፡ ከአንደበተ ርቱዕ ሰዎች በማይጠበቅ መልኩ ‹‹የገማ፣ የበከተ፣ የበሰበሰ፣ ደደብ…›› የሚሉ ስድቦችን በሕዝብ ፊት ደጋግመው ተሳድበዋል፡፡

አሁን መለስ ሞተዋል፡፡ ቀብራቸው በእልፍ ሺህ (እውነት እየተነጋገርን አይደል፤ ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ተወላጆች፣ ወደሩብ  በሚጠጉ አባሎቻቸውና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች እና ወደሩብ በሚጠጉ ግራ የገባቸው ሰዎች) አጀባ፣ በኢቴቪ እና ሬዲዮዎች ፕሮፓጋንዳ ይካሄዳል፡፡ የፕሮፓጋንዳው መዓት ‹‹ሳያዩ የሚያምኑትን›› ብዙሐን ኢትዮጵያውያንን ለኢሕአዴግ እንደሚመለምል አልጠራጠርም፡፡ ቢሆንም ግን መለስ ሲሞቱ (የመሪ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው በማለት) ንቄው የነበረውን የሕልፈታቸውን ብስራት ዛሬ አግኝቸዋለሁ፡፡

ከመቶ፣ ሁለት መቶ ዓመት በኋላ መለስ ሲታወሱ በሕንፃና ቀለበት መንገድ ሊታወሱ አይችሉም፣ ዘመኑ አይፈቅድላቸውም፡፡ የኤርትራ ጉዳይም ቢሆን አሉታዊ ነው፡፡ ሊታወሱ የሚችሉበት አንድ ብቸኛ አማራጫቸውን ተፈጥሮ ነጥቋቸዋል፡፡ መለስ ሦስት ዓመት ቢቆዩና እንዳሉትም ስልጣን ቢለቁ ኖሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ስልጣኑን ‹‹በፈቃዱ›› የለቀቀ የመጀመሪያው መሪ ይሆኑ ነበር፤ አመለጣቸው፡፡